ደ/ብርሃን ጤና ሣይንስ ኮሌጅ በተለያየ ሙያ ለ21ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ፡፡
ደ/ብርሃን ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ሐምሌ 16/2014 ዓ.ም. የተማሪዎች የምረቃ በዓል አከናውኗል፡፡የኮሌጁ መመህራንና ሠራተኞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች እና የተመራቂ ቤተሰቦች በተገኙበት ነው የምርቃት ስነስርአቱ የተካሄደው፡፡ የኮሌጁ ምክትል ዲን መምህር ሔኖክ ዲታ ባደረጉት ንግግር በመከላከል ላይ የተመሠረተውን የሀገራችን የጤና ፖሊሲ ከመተግበር አንጻር ኮሌጁ ለሀገራችን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሌጁ በ2014 ዓ.ም በነርሲንግ ፣ በፋርማሲ ፣ በሚድዋይፍ ፣ በላብራቶሪ ፣ በኢንቫይሮመንታል ኸልዝ ፣ በጀነሪክና አፕግሬድ ጤና ኤክስቴንሽን እና በአንስቴዥያ ሙያ በመደበኛ የትምህርት መስክ ያሰለጠናቸውን 726 የጤና ባለሙያዎች አስመርቋል።
ከነዚህ ተመራቂዎች ውስጥ 90 በመቶ ሴቶች መሆናቸውንና የዛሬዎቹን ሳይጨምር ከዚህ በፊት በተለያዩ ዙሮች 5 ሺህ 728 ተማሪዎች በማሰለጠን ለሥራ አሰማርቷል ሲሉ የኮሌጁ ምክትል ዲን መምህር ሔኖክ ዲታ ተናግረዋል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል ጤና መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ፀዳለ ሰሙንጉሥ እንደተናገሩት የጤናው ሴክተር መከላከልን መሠረት ያደረገ ፓኬጅ በመተግበር ሞዴል የሆኑ የጤና ተቋማትና በመገንባትና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን በማሰማራት ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ በዚህም እናቶች ከቅድመ ወሊድ ጀምሮ በጤና ተቋማት እንድወልዱ በማድረግ በወሊድና ተያያዥ ምክንያቶች እንዳይሞቱ በማድረግ የእናቶችንና ሕጻናትን ሞት በመቀነስ የድርሻውን እየተወጣ የሚገኝ ሲሆን የዛሬ ተመራቂዎችም ለጤናው ዘርፍ ተጨማሪ አቅም ናችሁ ሲሉ የክብር እንግዳዋ ተናግረዋል።
ተመራቂዎች ከኮሌጁ በትምህርት ያገኛችሁትን ዕውቀት ከምርቃት በኋላ በተከበረው የጤና ሙያ ወደሥራ ስትሰማሩ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ዘር ፣ ብሔርና ቀለም ሳትለዩ ርኅራኄና ትህትና የተሞላበት አገልግሎት በመስጠት የገባችሁትን ቃለ መሐላ ተግባራዊ ማድረግ አለባችሁ በማለት ወይዘሮ ፀዳለ አሳስበዋል።